×
Director Asmare Yigezu

የመንግስት ግዥ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መልዕክት

ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመነ የአሰራር ስርዓት እንዲኖራት እና ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል “ዲጂታል ኢትዮጵያ” የተሰኘ ዕቅድ ነድፋ የብልጽግና ጉዞ ጀምራለች፡፡ አገልግሎታችንም እንደ ሀገር የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት እና የተቋቋመበትን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ የፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶችና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የሚጠቀሙባቸውን የማዕቀፍ ስምምነት እና ስትራቴጅክ ግዥዎችን በመንግስት የኤሌክትሮኒክ የግዥ (e-GP) ስርዓት ግዥ በመፈፀመ እንዲሁም እንዲወገዱ ውሳኔ የተሰጠባቸው የመንግስት መ/ቤቶች የተለያዩ ንብረቶችን በተቀላጠፈ አኳኋን በሽያጭ በማስወገድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት አገልግሎታችን አሠራሩን በማዘመንና ዲጂታላይዝ በማድረግ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚፈፅማቸው የማዕቀፍ ስምምነት እና አገራዊ ስትራቴጃዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግዥዎች ከጥቅል ግዥ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ይበልጥ የሚያረጋግጡ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ የሀብት ስርጭትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እንዲያስችል የሚወጡ የግዥና የንብረት ማስወገድ ጨረታዎች ተደራሽነት፣ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በሌላ መልኩ ዜጎች የተዘረጋውን የዲጂታል አሠራር በመጠቀም ባሉበት ሆነው የአገልግሎታችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የጊዜና ገንዘብ ብክነት የሚቀንስና የርቀት ተግዳሮትን የሚያስቀር ይሆናል፡፡ ይህንን አሰራር እውን በማድረግ በአገልጋይነት መንፈስ ተገልጋዮቻችንን ለማገልገል በሙሉ ልብ የተዘጋጀን መሆኑን ስንገልጽ በብዙ ደስታ ነው፡፡ በተጨማሪም ተቋማት የሚፈፀሙት ግዥም ሆነ የንብረት ማስወገድ ስራው ከአካባቢ ብክለት የፀዳ እና ዘላቂነት ያለው መሆን እንዳለበት መንግስት በዘረጋው የGreen Procurement Policy መሰረት አገልግሎታችንም ፖሊሲውን በመደገፍ በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ግዥ እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እንዲሁም ”ፅዱ ተቋምን በመፍጠር ፤ ሀብትን እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ያላግባብ የተከማቹ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘት በተጨማሪ ተቋማትን ካላስፈላጊ የንብረት ክምችት ፅዱ በማድረግ ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ለአገር ውስጥ አምራቾች ልዩ ድጋፍ እና አስተያየት በማድረግ የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ አገልግሎታችንም በመንግስት የተሰጠውን ልዩ አስተያየትና ድጋፍ መሰረት በማድረግ ለተቋማት የሚፈፅማቸውን የጋራ መጠቀሚያ እና አገራዊ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ዕቃዎች ከአገር ውስጥ አምራቾች ግዥ እየፈፀመ ይገኛል፡፡ ይህም የአገር ውስጥ አምራቾችንና ምርትን ከማበረታታት በተጨማሪ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪን በመቀነስ መንግስት ለግዥ የሚያውለውን ገንዘብ ለሌላ ልማት እንዲያውለው ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ ሆኖም የአገር ውስጥ አምራቾች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ተወዳዳሪ እና ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመጨረሻም አገልግሎታችን አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ ግልጽ፣ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ያስቀመጠውን ተልዕኮ እንዲያሳካ የፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአቅራቢ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለተገልጋዮቻችን!

– ክቡር አቶ አስማረ ይገዙ